ሕዝቤ ሆይ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ
በርህን ከኅላህ ዝጋ ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ቀን ተሽሽግ
ኢሳ 26፡ 20

ያለ ቀጠሮ በዓለም ላይ ድንገት የተከሰተውን ይህን የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ-19 (በእግዚአብሔር ዓለም ብቻ ቀድሞ የታወቀውን) ሳስብ በአዕምሮዬ የሚመላለሱ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ በሰሜን አሜሪካ ካስከተለው በጎ ገጽታ አንዱና ዋናው ስው ሁሉ በግድ በቤቱ እንዲከት መደረጉ ነው ። ባልና ሚስት በገዛ ቤታቸው በፈረቃ በሚኖሩበት ሀገር ብዙዎች በቤታቸው የሚኖሩ ሳይሆን ለቤታቸው በሚኖሩበት ማለትም የቤት ኪራይ ፣ የቤት እዳ ለመክፈል ብዙውን ጊዜያቸውን ከቤታቸው ውጭ ተገደው በሚያሳልፉበት ቤት አለኝ የሚሉና በቤታቸው ግን የማይኖሩ ብዙ በሆኑበት ፤ አብዛኛው ሰው በሩጫ ማሽን ላይ እንዳለ ያለ እረፍት በሚሮጥበት ወላጆች ከልጆች ጋር በቂ ጊዜ ሳይኖራቸው ልጆች የሚያድጉበት ከዚያም ራስ ችለው ለብቻቸው ወደሚኖሩበት ደረጃ በሚደርሱበት የአኗኗር ዘይቤ በምንኖርበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ። አንድ ወዳጄ ከልጆቼ ጋር በቂ ጊዜ ሳላሳልፍ አደጉብኝ (አደጉልኝ ሳይሆን) እንዳለው ማለት ነው ።

ላልተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሁላችን በቤታችን እንድንሰበሰብ የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሮብናል:: ስለዚህ እንዲህ አይነቱ ጊዜ ለጌታ ልጆች አስገዳጅ እረፍት (Forced Leave )እንደሚሉት አስገዳጅ የጥሞና ጊዜ ፣ የጸሎት ፣ የጾም ጸሎትና ከቃሉ ጋር ሕብረት የማድረጊያ እርሱ የፍቅር አምላክ ቢሆንም እንደቤተሰብ እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት የማደሻ ጊዜ አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን ።

እንደሚታወቀው በቅጽበት ከውሃና ከመንፈስ ዳግም የተወለደው ማንነታችን የሚያድገው በሂደት ነው ለማደግ ደግሞ ከሚያስፈልጉን ነገሮች ዋናው መንፈሳዊ ስነምግባር ነው:: ገና ወደ ጌታ በመጣንበት (በእርግጥ እሱ ነው ወደኛ የመጣው) በዚያ የተባረከ የክርስትና የመጀመሪያዎቹ አመታት እናደርጋቸው የነበሩ በማለዳ ተነስቶ መጸለይ ቃሉን ማንበብ መጾም መጸለይ ከቅዱሳን ጋር ሕብረት ማድረግና የመሳሰሉት ነገሮች ሳናውቀው ቀስ በቀስ ከኛ ተወስደውና በሌሎች ነገሮች ተተክተው ያለን የምንመስል የወደቅን ከሆንን ሰነባብተናል ። እናም ይሄ ጊዜ እንደገና የጣልናቸውን እነዚህን እንቁዎቻችንን ለማንሳትና ከጌታ ጋር ያለንን ቃል ኪዳናችንን ለማደስ ወላጆች ለልጆቻችን እነዚህን መንፈሳዊ ስነምግባሮች (Spiritual Discpline ) ለማስተማር እንደ ባልና ሚስትም የተተዉ ወይም ያልነበሩን ለመንፈሳዊ እድገቶቻችን ወሳኝ የሆኑትን ነገሮች ለመጀመርም ይሁን ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ ነው እያልኩ ሰውነታችን ያስለመድነውን ነገር ለመልመድና እሱን ለመሆን የተሰራ መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልጋል :: እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ ተብሎ እንደ ተጻፈ ።

በመጨረሻም አንድ ወንድም ያለኝን አንስቼ ልጨርስ ለአገልግሎት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ በሄደበት ጊዜ በእንግድነት ካሳረፉት ቤተሰብ ጋር የተለያዩ ሰዎችን እያነሳን አገልጋዮችንም ጭምር ስንጫወት ፣ አስተያየት ስንሰጥ ፣ አንዳንዶቹንም ስንተች ቆይተን በመጨረሻም መንፈሴ ቆሽሾ አገኘሁት ። ከዚያ በኅላ ለራሴ ቃል ገባሁ የትም ሃገር ልሂድ ላንድ ሳምንትም ይሁን ላንድ ወር በምቆይበት ቤት ቅዱሳት መጽሓፍትን አብሬያቸው ላጠና ሌላውን ጉዳይ በልክ ላደርግ እንዳለው እኛም ዛሬ ያገኘነውን መልካም አጋጣሚ መቼ ሊያልቅ እንደሚችል አናውቅምና በሁሉም አቅጣጫ ፍሬያማ የምንሆንበት ለማህበራዊ ሚዲያዎች የምንሰጠውን ጊዜ በልክ አርገን የጌታን ፊት የምንፈልግበት የተሃድሶ ጊዜ እንዲሆን ምኞቴም ጸሎቴም ነው ።