ጌታ አጋንንት ደፋልኝ !

 

ቅርብ ጌዜ ይሄ Covid-19 እንዲህ እንቅስቃሴውን ሳይገድበው ብዙ አገልጋይ ወዳቾቼ ከኢትዮጲያ እኔ ወዳለሁባት አገር ብቅ ይሉ ነበር ። እናም ከነዚህ መካከል ካንዱ ጋር ሻይ ቡና እየተባባልን የሆድ የሆዳችንን እየተጫወትን በመሃል አገልግሎትህ እንዴት ነበር ? አልኩት ያው የመድረኩን ማለቴ ነው እንጂ እውነተኛውና ለአእምሮ የሚመቸውማ ሁለንተናን ከሌላው ከልክሎ የጌታ ብቻ ማድረግ እንደሆነ የተገለጠ ነው ፤ ቀበል አድርጎ የሰጠኝ መልስ አስደመመኝ በጣም ጥሩ ነበር ካለኝ በኋላ ጌታም አንድ ሁለት አጋንንት ደፋልኝ ! አለኝ ። አሜን ጌታ አሁንም ለዘላለምም እርኩሳን መናፍስትን ይድፋቸው ብዬ ግን ጌታ አጋንንትን የሚደፋቸው ( ከሰዎች ውስጥ እንዲወጡ )የሚያደርጋቸው ለእኛ ለአገልጋዮቹ ጥቅም ሆነ እንዴ ? አልኩኝ ለካስ እውነቱን ነው ያገልግሎታችን ተቀባይ፣ፈራጅ፣መዛኙና ዋጋን ከፋዩ ጌታ መሆኑ ቀርቶ አገልጋይን ‘አደገኛ!’ሲለንም ‘ዝም ብሎ!’ እያልን ደረጃ መዳቢዎች ከሆንን ከርመናል አገልጋይም አገልግሎቱን መዛኙና በመጨረሻም ዋጋ አስረካቢው ጠሪው መሆኑን ዘንግቶ የዘመኑን ሚዛን ለመድፋት አሳሩን የሚበላው ለዚሁ ነው ግን ይሄ ማለት አገልጋዮች የማይጠየቁ ፣ አይነኬዎች ናቸው ማለቴ አይደለም በዋናነት ተጠሪነታቸው ለጠሪውና በኋላም ለጠያቂው መሆን ግን አለበት እላለሁ ።

    

ለካስ ይሄም ወዳጄ ወዶ አይደለም የጌታን ከሱ ጋር መሆን ‘የአደገኛ’፣ ‘የሃይለኛ’አገልጋይነት ማሳያ ከሆኑት መካከል (በዚህ ዘመን)አንዱ ምልክት ባገልግሎቱ መገለጡ አስደስቶት የነገረኝ ። ቀድሞማ ይሄ እንደ ቃሉ የአማኝ ሁሉ ምልክት ነበር ። አሁንስ ቢሆን ቃሉ መች አረጀና !

 

እንግዲህ በዚህ ጊዜ በውስጤ አንድ ነገር አቃጨለብኝ ። ዋጋዬ ስንት ይሆን ? እነሆ በቶሎ እመጣለው ያለው ጌታ አሜን! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና !ብለን ሳንጨርስ ለእያንዳንዱ እንደስራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ በእኔ ዘንድ አለ ። ራእይ 22:12 ብሎ ነቃ ያደርገናል ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ የኖርነው ሕይወትና አገልግሎት ውጤት የሚታየው በጌታ መገለጥ እንደሆነ እያሰብን የአያንዳንዳችን ዋጋም በእጁ ነውና በዚህ ዘመን የተጋነነ ሙገሳ በሚሰጡን (OVER VALUE )በሚያደርጉን ልባችን ሳይግል ደግሞም በሚያንኳስሱን(UNDER VALUE) በሚያደርጉን ልባችን ሳይዝል የዋጋችን ባለቤት የሆነውን የጌታችንና የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ በናፍቆት እየጠበቅን ከጌታ መቀበላችንን እርግጠኛ በሆንበት ነገር ሁሉ በትጋት እናገልግል መልዕክቴ ነው ።

 

ሻሎም !

 

በጌታ ወንድማችሁ

ኤልያስ ተ/ሚካኤል

Check out this episode! || ይህንን ክፍል ይመልከቱ!