የወንበዴዎች ዋሻ !!

በመንገድ ለሚያልፍ ስው ወይም ከርቀት ከፍ ብሎ የተሰቀለውን የመስቀል ምልክትና በጥሩ ስም የታጀበ የማስታወቂያ ሰሌዳ ለሚመለከት እውነትም ቤቱ ቅዱስ ቤት ደግሞም መቀደሻ ‘ቀ’ ጠብቆ ይነበብ ይመስላል ምክኒያቱም ቤቱ ቅዱስ ነውና ከተገኘበት ቅዱስ መንፈስ የተነሳ እግዚአብሔር አብ ሕዝቡን የሚናገርበት ፤ ቅዱስ አምላክ ሕዝቡን የሚቀድስበት ፤ ደግሞም ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ። እንደሚታወቀው ደግሞ ጸሎት ከሚፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አንዱና ዋናው ንጹህ ልብ ነው ። ብሂሉስ ” ‘ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት ‘ ” አይደል የሚል እንዴት ተደርጎ ነው ጸሎትን ያለ ንጹህ ልብ ልናስበው የምንችለው እንዲያው ድከሙ ብሎን ካልሆነ በቀር ።
እንግዲህ ይህንን ቅዱስ ቤት ነው ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ ይዞ ለማጽዳት ሲነሳ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ” ተብሎ ተጽፋል እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ ‘ አደረጋችሁት ያላቸው ። እውነትም እንደ እግዚአብሔር ቤት ያለ ለወንበዴ የሚመች ጥሩ መመሸጊያ የት ይገኝ ይሆን ምክኒያቱም ሌባና ወንበዴ ሊገኝበት ይችላል ተብሎ የማይጠረጠር ቅዱስ ቦታ ነውና ። ከውጭ ለሚመለከተው የመስቀሉን ምልክት ሲያይ በዚህ የተሰበሰቡት የክርስቶስ ተከታዮች ፤ የመስቀሉ ቃል አማኞች ፤ ደግሞም ራሳቸውን የካዱና መስቀላቸውን ተሸክመው ዕለት ዕለት የሚከተሉ ናቸው እንደሚል ደግሞም ልንሆን የተገባን እሱኑ ሆኖ ሳለ ወደ ውስጥ ሲገባ የተጧጧፈ ንግድ ፣ ክፋትና ርኩሰት ፤ ጥላቻና ቂም በቀል የነገሰበት ፣ የቤቱ ባለቤት የተገፋበት ሆኖ እንዳይገኝ በነፍስ ወከፍ ከተያዝንበት ውንብድና እራሳችንን በቃሉና በመንፈሱ እያጸዳን የጌታን ማህበር የወንበዴዎች ዋሻ ከመሆን እንጠብቅ ያለዚያ ቤቱ እንዲያው የተተወ ፣ ችላ የተባለ ፤ ቢመስልም ባለቤት አለው ። ባለቤቱ ደግሞ ቅዱስ የሆነ ፤የገዛ ደሙን ያፈሰሰ ነውና ጅራፍ ማንሳቱ አይቀርም ። ቤቱ ዛሬም ቢሆን የጸሎት ቤት እንጂ የወንበዴዎች ዋሻ አይደለም !!

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ሻጮችን ከዚያ አስወጣ ደግሞም ” ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ ‘ አደረጋችሁት ” አላቸው ። (አመት)

ሉቃ 19፥ 45-46


ጌታ ይርዳን
የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛልን !